Numbers 9

የፋሲካ በዓል

1ከግብፅ ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን በሲና ምድረ በዳ ተናገረው፤ እንዲህም አለው፤ 2“እስራኤላውያን በተወሰነው ጊዜ የፋሲካን በዓል እንዲያከብሩ አድርግ፤ 3በዓሉንም በዚህ ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ በተወሰነው ሕግና ሥርዐት መሠረት ሁሉ አክብሩ።”

4ስለዚህ ሙሴ ፋሲካን እንዲያከብሩ ለእስራኤላውያን ነገራቸው፤ 5እነርሱም በመጀመሪያው ወር፣ በዐሥራ አራተኛውም ቀን ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ በሲና ምድረ በዳ ፋሲካ አደረጉ፤ እስራኤላውያን እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሁሉንም አደረጉ።

6አንዳንዶቹ ግን የሰው ሬሳ በመንካታቸው በሥርዐቱ መሠረት ረክሰው ስለ ነበር በዚያን ዕለት የፋሲካን በዓል ማክበር አልቻሉም፤ ስለዚህም በዚያኑ ዕለት ወደ ሙሴና ወደ አሮን መጥተው፣ 7ሙሴን፣ “በሬሳ ምክንያት ረክሰናል፤ ታዲያ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መሥዋዕት ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋር ሆነን በተወሰነው ጊዜ እንዳናቀርብ ለምን እንከለከላለን?” አሉት።

8ሙሴም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እናንተ የሚያዝዘውን እስካውቅ ድረስ ጠብቁ” ሲል መለሰላቸው።

9ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 10“እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ከእናንተ ወይም ከዘሮቻችሁ ማንኛውም ሰው በሬሳ ምክንያት ቢረክስ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ፋሲካ ማክበር ይችላል፤ 11ይህንም በሁለተኛው ወር፣ በዐሥራ አራተኛው ቀን ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ ያክብሩ፤ የፋሲካውንም በግ እርሾ ከሌለበት ቂጣና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት። 12እስኪነጋ ድረስ ከዚህ ምንም አያስተርፉ፤ ከዐጥንቱም ምንም አይስበሩ፤ ፋሲካን በሚያከብሩበት ጊዜ ሥርዐቱን በሙሉ መጠበቅ አለባቸው። 13በሥርዐቱም መሠረት ንጹሕ የሆነ ወይም ሩቅ መንገድ ያልሄደ ሰው ፋሲካን ሳያከብር ቢቀር፣ ያ ሰው የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መሥዋዕት በተወሰነው ጊዜ አላቀረበምና ከወገኖቹ ፈጽሞ ይለይ፤ ያም ሰው የኀጢአቱን ዋጋ ይቀበላል።

14“ ‘በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ፋሲካ ለማክበር ቢፈልግ በሕጉና በሥርዐቱ መሠረት መፈጸም አለበት፤ ለመጻተኛውም ሆነ ለአገሬው ተወላጅ የሚኖራችሁ ሕግ አንድ ይሁን።’ ”

ከማደሪያው በላይ የነበረው ደመና

15ማደሪያው በተተከለ ዕለት ደመናው የምስክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ከምሽት እስከ ንጋት ድረስ ማደሪያውን የሸፈነው ደመና እሳት ይመስል ነበር። 16ይህ በዚህ ሁኔታ ቀጠለ፤ ደመናው ማደሪያውን ሸፈነው፤ በሌሊትም የእሳት መልክ ነበረው። 17ደመናው ከድንኳኑ ላይ በሚነሣበት ጊዜ እስራኤላውያን ጕዟቸውን ይጀምሩ ነበር፤ ደመናው በሚቆምበት ቦታ ደግሞ ይሰፍሩ ነበር፤ 18እስራኤላውያን ጕዞ የሚጀምሩትም ሆነ የሚሰፍሩት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ነበር። ደመናው በድንኳኑ ላይ በሚቈይበት ጊዜ ሁሉ ከሰፈር አይንቀሳቀሱም ነበር። 19ደመናው በድንኳኑ ላይ ብዙ ቀን ቢቈይም እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ትእዛዝ ይጠብቃሉ እንጂ ተነሥተው አይጓዙም። 20አንዳንድ ጊዜ ደመናው በድንኳኑ ላይ የሚቈየው ለጥቂት ቀን ብቻ ነበር፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ይሰፍራሉ፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ጕዞ ይጀምራሉ፤ 21አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ደመናው ከምሽት እስከ ንጋት ብቻ ይቈያል፤ ደመናው ንጋት ላይ ሲነሣም ጕዟቸውን ይጀምራሉ፤ ቀንም ይሁን ሌሊት ደመናው ከተነሣ ጕዞ ይጀምራሉ። 22ደመናው በድንኳኑ ላይ ለሁለት ቀንም ይሁን ለወር ወይም ለዓመት ቢቈይ፣ እስራኤላውያን በሰፈር ይቈያሉ እንጂ ጕዟቸውን አይቀጥሉም። 23በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ይሰፍራሉ፤ በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ትእዛዝ ይጓዛሉ፤ እነርሱም በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር።

Copyright information for AmhNASV